በሀረሪ ክልል በከተማ ግብርና ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተጠቆመ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በከተማ ግብርና ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተደድር ሚስራ አብደላ ገለፁ።

በክልሉ 40 ሄክታር መሬት በከተማ ግብርና እየለማ መሆኑን ተጠቁሟል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ ለዋልታ እንደገለፁት በክልሉ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንቅናቄ መልክ እየተከናወነ የሚገኘው የከተማ ግብርና መርሃ ግብር አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል።

መርሃ ግብሩ ተዳክሞ የቆየውን የክልሉ የከተማ ግብርና እንቅስቃሴን ለማነቃቃት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯልም ብለዋል።

የዘር አቅርቦት በማሟላት የከተማው ነዋሪም ሆነ ተቋማት ባላቸው ክፍት ቦታ እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በዘንድሮው አመት 37 ሄክታር መሬት በከተማ ግብርና ለማልማት ታቅዶ 40 ሄክታር መሬት በማልማት ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ይህም ህብረተሰቡን ላይ የበለጠ መስራት ከተቻለ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያመላከተ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በቀጣይም የውሃ እና የዘር አቅርቦትን በማጎልበት የበለጠ ውጤት እንዲገኝና ሕዝቡ በምግብ ራሱን እንዲችል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በከተማ ግብርና የተሰማሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው ባመረቱት ምርት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ጫናን ከመቋቋም አንፃር ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)