በሀረሪ ክልል የንግድ ማህበረሰብ ለሰራዊቱ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

መስከረም 9/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ ለመከላከያ ሰራዊት በመጀመሪያው ዙር ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በሚደረግበት ዙሪያ በክልሉ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ሚስራ አብደላ እንደተናገሩት አሸባሪው ህውሃት መንግስት የሰጠውን የሰላም አማራጭ በመግፋት በሀገሪቱ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቷል።

በመሆኑም የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት ሁሉም በመተባበርና በመተጋገዝ የበኩሉን መወጣት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የግል ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ ለመከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በእለቱ ላደረጉት ድጋፍም በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል።

በቀጣይም ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ባለሃብቶች በሰጡት አስተያየትም በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ በጋራ በትብብር መመከት ያስፈልጋል።

በተለይም የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የሀገርና ህልውና እየታደገ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት መደገፍ የዜግነት ግዴታ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)