በሀረሪ ክልል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 42 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሐምሌ 30/2016 (አዲስ ዋልታ) በሀረሪ ክልል ከሰሞኑ ይፋ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 42 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ።

የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ትከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የቁጥጥር እና ክትትል ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ኃላፊ ሸሪፍ ሙሜ እየተከናወነ ባለው የክትትል ስራ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ግብር ኃይል በማቋቋም እስካሁን ባለው ከ 2 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የቁጥጥር ስራ በማከናወን ያለ አግባብ ዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 35 የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መታሸጋቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል 244 የንግድ ተቋማት ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው 7 ነጋዴዎች በህግ ተጠያቂ መደረጋቸውን እንደገለጹ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

በክልሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርት በመሰወር ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን ለመቆጣጠር በሁሉም ወረዳዎች ግብር ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን የጠቆሙት ኃላፊው ህብረተሰቡ ሕገ ወጦችን በማጋለጥ እያደረገው ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።