በሀረሪ የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል

ጥር 8/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የከተራና የጥምቀት በዓል ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ጥላሁን ዋደራ ለዋልታ እንደገለፁት በክልሉ የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ አካላት በቂ ዝግጅት አድርገዋል።

ለዚህም የክልሉ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

በክልልና በወረዳ ደረጃ ከተለያዩ ሀይማኖት አባቶች፣ ከሰላም አደረጃጀቶች፣ ወጣቶችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ፍተሻዎችና ጥበቃዎች እንዲጠናከሩ መደረጉን ነው የተናገሩት።

በአካባቢው በብሔርና በሀይማኖት መካከል ችግር እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት ስለመኖራቸው ያነሱት የቢሮ ኃላፊው ህዝቡ በፀጥታ ስራው ላይ እያደረገ የሚገኘውን የላቀ አስተዋጽኦ በማጠናከር የእነኚህ አካላትን ፍላጎት እንዳይሳካ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተስተዋለ ለሚገኘው አንፃራዊ ሰላም የህዝቡ ሚና የላቀ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም የክልሉን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ሰላም ወዳዱ ህዝብ እያደረገ የሚገኘውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)