በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሠራል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)


ሐምሌ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ በሀገረ መንግስት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ መድረኮችን ሲያመቻችና የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት “ጥምረት ለሴቶች ድምፅ” ለብሄራዊ ምክክሩ የሰበሰበውን የሴቶችን አጀንዳ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባስረከበበት ጊዜ ነው፡፡

በርክክቡ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ መንግስት ባለፉት ዓመታት አጥብቆ ሲሰራበት የቆየውና ዜጎችም ለዘመናት ሲጠየቁ የኖሩት በሀገራዊ ምክክር አማካኝነት መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሳቤ አሁን ላይ ወሳኝ ሊባል በሚችል ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽዖ ስለሚያበረክት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ ካለፈው መጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት በስምንት ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በመዘዋወር በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር የተሻለ ሀገር በመገንባትም ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አጀንዳዎቹ የአሁንና የወደፊት ሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዋና መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት አሸናፊ ሆነን እንውጣ ከተባለ መመካከር አለብን በምክክሩም ሴቶችን ይዘን መውጣት አለብን። የሴቶች አጀንዳ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነውም ብለዋል።

የሴቶችን አጀንዳ ለብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዋና መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) የ’ጥምረት ለሴቶች ድምጽ’ ስራ አስፈፃሚዎች ማስረከባቸውንም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡