በሀገር ክህደት ወንጀል በቁጥጥር ስር በዋሉት ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ ከአወጣባቸዉ አመራሮችና የጦር መኮንኖች መካከል በቁጥጥር ስር በዋሉት ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑንና በየጥሻውና በየጉድጓዱ የተደበቁትንም በማደን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሚያካሄዱት የህግ ማስከበር ዘመቻ በጁንታው የህወሃት ቡድን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሳተፍ የጥፋት ስራው አካል ናቸው ብሎ በጠረጠራቸው ከ3 መቶ በላይ ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት መውጣቱ ይታወቃል፡፡

በዚህም እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል፡-

  1. ሜ/ጀኔራል ገ/መድህን ፈቃዱ ሀይሉ
  2. ሜ/ጀኔራል ይዳው ገ/መድህን
  3. ብ/ጀኔራል ገ/ህይወት ሲስኖስ ገብሩ
  4. ብ/ጄኔራል ኢንሱ እጃጆ እራሾ
  5. ብ/ጄኔራል ፍስሃ ገ/ስላሴ
  6. ኮ/ል ደሳለኝ አበበ ተስፋዬ
  7. ኮ/ል እያሱ ነጋሽ ተሰማ
  8. ኮ/ል መብራቱ ተድላ ወ/ሚካኤል
  9. ኮ/ል ባራኪ ጠማሎው ገብሩ
  10. ኮ/ል ሀይላይ መዝገብ ማሾ
  11. ኮ/ል ፍሰኃ ግደይ ወ/ማርያም
  12. ሌ/ኮ/ል ሙዘይ ተሰማ ስዩም
  13. ሌ/ኮ/ል ፍሰሃ በየነ ገ/ኪዳን
  14. ሌ/ኮ/ል ምሩጽ ወ/አረጋይ ገ/መስቀል
  15. ሌ/ኮ/ል ምሩጽ በርሄ አበራ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸዉ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው 81 የህወሀት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ የተያዘ መሆኑ ይታወቃል::

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሀገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ባካሄዱት የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በተካሄደው የምርመራ ስራ እንደተጣራው እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል፡-

  1. ኮ/ል ተስፋዬ ገ/መድህን
  2. ኮ/ል የማነ ገ/ሚካኤል
  3. ሌ/ኮ/ል ሀዲሽ ገ/ጻዲቅ
  4. ኮ/ል ማዕሾ
  5. ኮ/ል አለም ገ/መድህን የተባሉት እንደሚገኙበት ተረጋግጧል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ቀሪ ያልተያዙ የጦር መኮንኖችንና የህወሀት አመራሮችን ከየተደበቁበት ጥሻ፣ ዋሻ እና የሀይማኖት ስፍራዎች በማደንና በመልቀም ለህግ ለማቅረብ ቀን ተሌት እየሰራ ይገኛል፡፡

የጁንታው የህወሀት አመራሮች በውጊያ ከተሸነፉ በኃላ ራሳቸውን ካለባበስ ጀምሮ በመቀያየር ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ፖሊስ መረጃው ደርሶታል፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብ ህግ ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ እስከዛሬ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ኮሚሽኑ ምስጋና እያቀረበ ያልተያዙትን ተፈላጊዎች ከተደበቁበት ቦታ ይዞ ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፖሊስ አባላት ጎን በመቆም እና አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

ታህሳስ 27/ 2013 ዓ/ም

አዲስ አበባ