በሁለት ዓመታት ከ24 ቢሊየን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ መደረጉ ተገለጸ

መንግሥት ከ2011 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም ጭማሪውን በመሸፈን ላለፉት 2 ዓመታት 24.05 ቢሊዮን ብር የዋጋ ጭማሪውን እየደጎመ መቆየቱን የኢፌዴሪ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢፌዴሪ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት የጥር ወር የነዳጅ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ ማድረጉንም አስታውቋል።

የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በጥር ወር የነዳጅ ምርት አቅርቦት ላይ መጠነኛ የዋጋ ክለሳ መደረጉን የገለጹት በሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት ናቸው።

በተጠናቀቀው የታኅሣሥ ወርም ምርቱ 1.5 ቢሊዮን ብር የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ሁሉንም የዋጋ ጭማሪውን ሸፍኖ ከሄደ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጸእኖ የሚያሳድር በመሆኑ መንግሥት 75 በመቶውን እንዲሸፍን እና ቀሪው 25 በመቶ በኅብረተሱ እንዲሸፈን ተደርጎ መጠነኛ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉን አብራርተዋል።

ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች የአቅርቦት እና ሥርጭትን በተመለከተ የጊዜ ሰሌዳቸውን ጠብቀው ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለኅብረተሰቡ እየተሰራጩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ላለፉት ስድስት ወራት ከ392 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እና 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር እና ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የ5 በመቶ ቀረጥ እየከፈሉ ምርቶቹን እንዲያስገቡ መደረጉንም ነው የገለጹት።

በቀጣይም የቀረጥ እና የታክስ ሁኔታዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደ አስፈላጊነቱ የሚታይበት ሁኔታም እንዳለ ተገልጿል።

አገሪቱ ከወጪ ንግዱ የምታገኘው የገቢ መጠን እና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ ምርቶች የምታወጣው የንግድ ሚዛን መጠን ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት አስፈላጊ በመሆኑ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህም የዘይት ምርት በአገር ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን እና 2 ፋብሪካዎች ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡ መሆኑን፣ ሌሎችም በቀጣይ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገው ጥረት በሌሎች የመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።