በሃሰተኛ ገንዘብ ነዳጅ ቀድቶ ለማምለጥ የሞከረው አሽከርካሪ ከተሽከርካሪ ጋር በመጋጨት ህይወቱ አለፈ

ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው ወልዴ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) በሃሰተኛ ገንዘብ ነዳጅ ቀድቶ ለማምለጥ የሞከረው አሽከርካሪ ከቆመ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨት ህይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

የትራፊክ አደጋው የደረሰው ትናንት ከሌሊቱ 6፡30 ሰዓት ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ተብሏል፡፡

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1- 30262 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ ከጀሞ 1 አቅጣጫ ወደ ሚካኤል አደባባይ እየተጓዘ 67 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጅ ሊቀዳ መግባቱን በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ቲም ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው ወልዴ ገልፀዋል፡፡

አሽከርካሪው ነዳጅ ከቀዳ በኋላ አምስት ባለ 100 መቶ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለነዳጅ ማደያው ሰራተኛ ሰጥቶ በሚሄድበት ወቅት ነዳጅ ቀጂው የብሮቹን ትክክለኛነት በመጠራጠሩ ሊያስቆመው መሞከሩን ምክትል ኢንስፔክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

አሽከርካሪው ግን በፍጥነት በማሽከርከር ለማምለጥ ጥረት ሲያደርግ መንገድ ዳር ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3A- 60203 አ.አ ከሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ አብረውት ተሳፍረው የነበሩ 2 ግለሰቦች ላይም ከባድ የአካል ጉዳት በመድረሱ ተጎጂዎቹ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ማስረዳታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW