በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው – ግብረ ኃይል

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) በሃይማኖት ሽፋን ግጭት በመቀስቀስ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ሃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ከቀብር ስፍራ ጋር በተያያዘ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ሃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቋል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ አጀንዳ በማሰራጨት ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ለማስገባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

ህብረተሰቡ ለአመታት በገነባው ጠንካራ የሆነ የጋራ እሴት ይህ ሙከራ የከሸፈባቸው ኃይሎች፣ ቀሪውን የሃይማኖት ካርድ በመምዘዝ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ መጠራጠርና ጥላቻ እንዲፈጠር ብሎም ወደ ግጭት እንዲያመራ በተለያዩ መንገዶች ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።

በጎንደር የተከሰተው ግጭት በተለያዩ ዕምነቶች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ወደ ሃገራዊ ቀውስ እንዲያመራ የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ በዚህ ድርጊት በተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ መወሰደ መጀመሩን ጠቁሟል።

በዚህ መሰረት በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል።

እንደ መግለጫው፤ በጎንደር የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎችም በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚጋብዙ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሃሰተኛ መረጃዎችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎችም የእምነት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግጭቱ ሃገራዊ ቅርጽ እንዲኖረው ሙከራ እየተደረገ ነው።

የፌዴራል የደህንትና የጸጥታ መዋቅር በድርጊቱ በሚሳተፉት ላይ ብቻ ሳይሆን ከኋላ በመሆን በሚዘውሩት ላይ በቂ መረጃና ማስረጃ ያለው በመሆኑ ተከታታይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ያስታወቀው መግለጫው፤ ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ የሚቀሰቅሱ፤ በተለይም ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም ሃሰተኛና የጥላቻ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት በህግ የሚጠየቁበት አግባብ መኖሩን የጠቆመው መግለጫው፤ በዚህ ህግወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ባስቸኳይ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም በጥብቅ አሳስቧል።

ኢትዮጵያውያን ለዓመታት የገነቡት በአብሮነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እኩይ ዓላማ ባነገቡ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ሃይሎች እኩይ ሴራ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት በሚፈጥሩት የግጭት አጀንዳ አይሸረሸርም ያለው መግለጫው፤ ህብረተሰቡ ለዘመናት ባዳበራቸው መልካም እሴቶች እንደዚህ አይነት የፈተና ወቅቶችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ በመፍታት እንደሚያስመሰክር የጋራ ግብረ ኃይሉ እምነት መሆኑንም ጠቁሟል።

ዛሬም ኢትዮጵያን ሌላ የግጭት አጀንዳ በመስጠት ለማተራመስ ሙከራ ቢደረግም በደኀንነትና በጸጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ጥረት በቁጥጥር ስር ውሏል ያለው የፌዴራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፤ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ችግሩ እንዳይስፋፋ ያደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!