በህወሓት መወገድ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከነበው ይልቅ በአንድነትና በሰላም በመጓዝ፣ የዴሞክራሲና የሰላም መሰረቶችን እንደምትገነባ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብረሃ ገለጹ።
አቶ ዛዲግ ከዶቸ ዌለ ኮንፍሊክት ዞን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ “መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይ ህዝብን ከጁንታው የህወሃት ቡድን የታደገ ነው” ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ቢጠየቅም ጁንታው ህወሃት ቡድን ግን ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ጦርነት መግባቱን ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቡድኑ የሚፈጥራቸውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሰፊ ጥረት ማድረጋቸውን አስታወቀው፤ ቡድኑ ግን የሽምቅ ተፋላሚዎችን ተግባር መፈጸሙን በመጥቀስ አስረድተዋል።
በዚህም የየትኛውም አገረ መንግስት የማይታገሰውን ጥቃት ክልሉን በመጠበቅ ላይ በነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ መፈጸሙን አስታውሰዋል።
ይህንን ተከትሎ መንግስት ከሃዲውን የጥፋት ቡድን በህግ ለመጠየቅ ዘመቻ አካሂዶ ማጠናቀቁንና አሁን የመልሶ ግንባታ ስራ ላይ መሰማራቱን አቶ ዛዲግ አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል በህወሃት ጁንታ ሃይል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመገንባትና፣ አስተዳደራዊ ስራዎችን መልሶ በማደራጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የህወሓት ጁንታ መወገዱ በመላው አገሪቱ ለሚካሄደው የዴሞክራሲና የሰላም እንዲሁም የልማት ግንባታ በር መክፈቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
“የቡድኑ መወገድ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከነበረው ይልቅ በአንድነት እንድትጓዝና የዴሞክራሲና የልማት ስኬት እንድታስመዘግብ ያስችላታል” ብለዋል።
በቀጣይም ሁሉን አቀፍ ዴሞክራሲያዊና ገለልተኛ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።