ሐምሌ 23፣ 2013 (ዋልታ) – በለንደን የተወለዱ እና ከ40 በላይ የሚሆኑ ታዳጊ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን በማስመለከት የቦንድ ግዢ እና የገንዘብ ስጦታ አበረከቱ።
ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት ቦንድ መግዛታቸውን ያመለከቱት ታዳጊ ወጣቶቹ ግድቡ እስኪጠናቀቅ የበኩላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በገቡት ቃል መሰረት የሁለተኛ ዙር የቦንድ ግዢና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።
ታዳጊዎቹ ከቤተሰቦቻቸው የሚሰጣቸውን የኪስ ገንዘብ እና ከተለያዩ ምንጮች ያገኙትን ገንዘብ በየአመቱ እየቆጠቡ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ለቦንድ ግዢ ማዋላቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ተስፋ ወጣቱ ትውልድ ነው ያሉት ታዳጊ ዳያስፖራዎች ባለን አቅም ሁሉ ሀገራችንን እንደግፋለን ብለዋል።
ታዳጊዎቹን የተቀበሉት በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በወቅቱ እንደተናገሩት ምንም እንኳን በእንግሊዝ ሀገር የተወለዳችሁ ታዳጊ ወጣቶች ብትሆኑም የዛሬው ተግባራችሁ ልባችሁ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያረጋገጣችሁበት ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል የሚኖረው ማንኛውም ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ወደፊት በእንግሊዝ ፖለቲካ ስርአት ውስጥ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደምትሰሩ እተማመናለሁ ብለዋል።