በሌጎስ የአክሰስ ባንክ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸነፉ

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ የተካሄደውን የአክሰስ ባንክ ሌጎስ ከተማ የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ አሸንፈዋል።

በሴቶች ዘርፍ በተካሄደው ውድድር አትሌት ስራነሽ ዳኜ አንደኛ ስትሆን፤ አትሌት አለምነሽ ሂርፓ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ  አጠናቃለች። ኬንያዊቷ ናኦሚ ማዮ በውድድሩ ሶስተኛ ሆናለች።

በወንዶች ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ኡልፋታ ዴሬሳ፤ ኬንያውያኑ ዴቪድ ባርማሲ እና ኢማኑኤል ናቤን በማስከተል አሸንፏል።

ኬንያዊው አትሌት ዴቪድ ባርማሲ ከሁለት አመት በፊት ባስመዘገበው (2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ) ጊዜ የሌጎስ ማራቶን የቦታው ክብረወሰን ባለቤት ነው።

የአክሰስ ባንክ ሌጎስ ከተማ ማራቶንን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ሲያሸንፉ እአአ ከ2019 በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በወቅቱ በወንዶች አትሌት ስንታየሁ ለገሰ እና በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት መሰረት ድንቄ አሸናፊ መሆናቸወን አስታውሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሌጎስ ማራቶን ውድድር እአአ በ2016 የተጀመረው ሲሆን በሴቶች ዘርፍ ከተካሄዱት ውድድሮች ኢትዮጵያውያኑ 5 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘዋል።

በተመሳሳይ ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያውያን ማሸነፍ የቻሉት ዘንድሮን ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።