በልደታ ክፍለ ከተማ የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – በተያዘው ዓመት በክፍለ ከተማው ሊሠሩ ከታቀዱ 83 ፕሮጀክቶች መካከል 74 የሚሆኑት ከተያዘላቸው ጊዜ በፊት ነው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁት ተብሏል ።
አጠቃላይ ወጪው 135.2 ሚሊየን ብር የሚሆነው 74 ፕሮጀክቶች ውስጥ 21ዱ ትምህርት ቤቶች ፣ አምስቱ ጤና ጣቢያ፣አምስቱ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች እና አራቱ የወጣት ማዕከላት መሆናቸው ተገልጿል።
በመርሀ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፅ/ቤት ሀላፊ እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሀላፊ አቶ መለስ አለሙ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ በወሰደው ቁርጠኝነት ህዝቡን በማሳተፍ የተገኘ ስኬት ነው ብለዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሕብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እየተሠሩ ላሉ ስራዎች የእነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ማሳያ ነው ብለዋል። ህዝቡን በማሳተፍም ቀሪ ስራዎችን ለመሥራት ክፍለ ከተማው በቀጣይም እንደሚሠራ ገልፀዋል።
(በድልአብ ለማ )