በሐምሌ ወር 8 ሺሕ ዩኒት ደም መሰብሰብ ተችሏል ሲል የደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ

ነሐሴ 4/2014 (ዋልታ) በሐምሌ ወር 11 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ 8 ሺሕ ዩኒት ደም መገኘቱን የኢትዮጵያ የደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ተናግረዋል።

ጊዜው የክረምት ወቅት እንደመሆኑ የደም መለገስ ተግባሩ በከፍተኛ ሁኔታ መቀዛቀዙን ኃላፊው ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በቀን ከ250 ዩኒት እስከ 300 ዩኒት ደም እየተሰበሰበ ቢሆንም ወደ ክልል ከተሞችና ለመንግስት ሆስፒታሎች በዛው ልክ እየወጣ በመሆኑ የደም እጥረት መከሰቱን ተናግረዋል።

የተከሰተው እጥረት እንደየ የደም ዓይነቱ የሚለያይ ቢሆንም በተለይ በፕላትሌት እና “O” በተሰኘው የደም ዓይነት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በደም ባንክ የደም እጥረት ሲያጋጥም በየሆስፒታሎች የደም ፍላጎት እንደሚጨምር ገልጸው በዚህ ፍጥነት አገልግሎት ማግኘት ያለባቸው ታካሚዎች መደራረብን ያመጣል ተብሏል።

ለአብነት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ በቀን እስከ 120 ዩኒት ደም እንደሚጠቀም ተገልጿል።

በርካታ ደም ከትምህርት ተቋማት እንደሚሰበሰብ የተናገሩት ኃላፊው፣ ጊዜው የትምህርት ተቋማት የተዘጉበት ወቅት በመሆኑ፣ የደም እጥረቱን ለመቅረፍ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በአቅራቢያው በሚገኙ የደም ባንክ መሰብሰቢያ ተቋማት ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።

ብሔራዊ የደም ባንክም በተለያዩ ቦታዎች ዘመቻዎችን በማድረግ ድንኳኖችንም በመትከል በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢብኮ ነው።

ተቋማትም የክረምት በጎ ፍቃድ መርሐግብር አካል አድርገው ችግኝ ሲተክሉ፣ ጎን ለጎን ደም ልገሳ እንዲያከናውኑ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።