በሐረሪ ክልል ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ጤና ጣቢያ ተመረቀ

ጥር 29/2014 (ዋልታ) በሐረሪ ክልል የጤና አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
በክልሉ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ጤና ጣቢያ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ርዕሰ መሰተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ለሕዝብ በገባው ቃል መሰረት የማኅበራዊና የምጣኔ ሃብት ጥያቄዎችን ለመመለስ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማጎልበትና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጤና ጣቢያ ይገንባልን ጥያቄው የአካባቢው ማህበረሰብ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቀው የቆየ መሆኑን አንስተው የፕሮጀክቱን የግንባታ ወጪ ለሸፈነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምስጋና አቅርበዋል።
ጤና ጣቢያው ኅብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ በማስቻል በተለይም የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።