በሐረሪ ክልል የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ አመራሩ መረባረብ ይጠበቅበታል ተባለ


መጋቢት 9/2014 (ዋልታ)
ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አመራሩ መረባረብ እንደሚጠበቅበት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ከክልሉ ሕዝብ ጋር በሚያደርገው ምክክር ላይ ዛሬ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሕዝብ ጋር የሚካሄደው ውይይት የጎላ ጠቀሜታ አለው።
ይህም አመራሩ በምርጫው ወቅት ለሕዝቡ በገባው ቃል መሰረት የተከናወኑ እና ክፍተት የሚታይባቸውን ሥራዎች በማመላከት አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
እንዲሁም በአመራሩና አስፈጻሚው ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በግልጽ የሚያሳይ እና ምላሽ ለመስጠትም የሚያግዝ አካሄድ እንደሆነና በአፈጻጸም የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከልና አመራሩም ኃላፊነቱን እንዲወጣ መንገድ የሚያመቻች መሆኑን አመላክተዋል።
ክፍተቶችን የሚያሳዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች በውይይቱ ማሳተፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዚህም በተለይ በውይይቱ ኅብረተሰቡን ባለቤት በማድረግ ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሃሳቡን እንዲሰጥ መደረግ አለበት ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ኅብረተሰቡ በክልል እና ፌዴራል ደረጃ እንዲፈታላቸው የሚነሱትን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አመራሩ ከወዲሁ በመዘጋጀት መረባረብ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም በበኩላቸው ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ውይይቱ መዘጋጀት በክልሉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለልና የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉ ሕዝብ በፌዴራል ደረጃ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ (ዶ/ር) ውይይቱ የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመለየት ለአስፈጻሚው አካል እንዲደርስ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በተለይ በፌዴራል ደረጃ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎችን የማደራጀት ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንዲደርስም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ለውይይቱ መሳካት የክልሉ ምክር ቤት አባላት እና ከወረዳ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮች እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በውይይት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ሚስራ አብደላ፣ የሐረሪ ጉባዔ አፈ ጉባዔ ሙህየዲን አህመድ፣ የብልጽግና ፓርቲ ተወካይና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።