በሐረሪ ክልል የዋጋ ንረትን የማረጋጋት ሥራ

ጳጉሜ 03/2013 (ዋልታ) በክልሉ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ የገበያ ዋጋን በማረጋጋት “የመልካምነት” አርዓያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ አስገነዘቡ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በክልሉ ከሚገኙ የደቡብ ክልል ተወላጆች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በመድረኩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ የክልሉ መንግስት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመሰረተ ልማት እና የመልካም አስተዳደር እና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት የንግዱ ማህበረሰብ በአገሪቱ ላይ ከውስጥና ከውጭ የተቃጣውን ሀገር የማፍረስ ሴራና ኢኮኖሚያዊ አሻጥርን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግስትን እና ህዝቡን እየተፈታተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረትን በማረጋጋት በኩል የንግዱ ማህበረሰብ የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት “የመልካምነት” ዓርዓያ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ በክልሉ የዋጋ ንረትን በመፍጠር አሻጥር የሚሰሩ የመንግስት ተቋማትንም ሆነ ስግብግብ ነጋዴዎችን የማጋለጥ ስራን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ጠቁመው፣ በቀጣይም እስከ ግንባር ድረስ በመሄድ ለሰራዊቱ አለኝታነታቸውን ለማሳየት እየተዘጋጁ እንደሆኑ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።