በሕወሓት የተፈጸመው ዝርፊያ የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ችግር እንደሚዳርገው ተገለጸ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) ሽብርተኛው የሕወሓት ታጣቂዎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የፈጸሙት ዝርፊያ የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ችግር የሚዳርግ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።

አሸባሪው ሕወሓት ትናንት በመቐሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን 12 ነዳጅ ቦቴ መዝረፉን የተባበሩት መንግሥታት መግለጹ ይታወቃል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምም የሕወሓት ታጣቂዎች የፈጸሙት ዝርፊያ አሳፋሪ መሆኑን ገልጸው ዝርፊያው በሰሜኑ ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ ችግር የሚዳርግ መሆኑንም አመላክቷል።

ላለፉት ጥቂት ወራት የነበረው የተኩስ አቁም የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ወደ 5 ሚሊየን ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ እንዲያደርሱ አግዟቸው እንደነበርም አስታውሷል።

ይሁን እንጅ በትናንትናው እለት በቡድኑ የተፈጸመው ዝርፊያ ይህን ሰብአዊ ድጋፍ አደጋ ላይ እንደጣለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ኃላፊ በተቋሙ ይፋዊ ድረ ገፅ በኩል ይፋ ባደረጉት በዚህ መግለጫ አመላክተዋል።

የአሸባሪው ሕወሓት ባለስልጣናት የዘረፉትን የነዳጅ ክምችት በአስቸኳይ እንዲመልሱ ያሳሰበው የአለም የምግብ ፕሮግራም የተወሰደው ነዳጅ በቅርቡ በድርጅቱ የተገዛና ከመሰረቁ ጥቂት ቀናት በፊት ወደ ቦታው የደረሰ መሆኑን ጠቁሟል።

ድርጅቱ ያለ ነዳጅ አቅርቦት የምግብ፣ ማዳበሪያ፣ መድሀኒት እና ሌሎች የአደጋ ጊዜ አቅርቦቶችን በትግራይ ማከፋፈል እንደማይችልም አሳስቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!