በሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ውይይቶች የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱጀባር መሀመድ ገለጹ፡፡
ኃላፊው በፓርቲው ድህረ-ጉባዔ በየደረጃው በተካሄዱ የሕዝብ ውይይቶች የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ አድርጎ በተዘጋጀው 90 ቀናት ዕቅድ ዙሪያ ከክልሉ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በዚህም ሕዝቡ በየደረጃው ትኩረት ሰጥቶ ያነሳቸው የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሌብነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የልማት እና ሌሎች ጥያቄዎች የዕቅዱ መነሻ ተደርገው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣዮቹ 90 ቀናት ውስጥ ሕጋዊ እርምጃን በማጠናከር ሰው ሠራሽ የገበያ አቅርቦት ችግርና የኑሮ ውድነትን ማስተካከል የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ያሳሰቡት ኃላፊው የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ከሌብነትና ከግል ተጠቃሚነት ነጻ በማድረግ የተገልጋዮችን አርካታ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አብዱልሀኪም ኡመር በበኩላቸው በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር ዕቀዱን መነሻ ያደረገ ውይይት ከመጋቢት 29 ቀን ጀምሮ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ሰፊውን ሕዝብ በማሳተፍ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሚያዚያ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ድረስ የሚፈጽም ልዩ እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸው ጥያቄዎቹ በጥራት፣ በፍጥነት እንድመለሱ በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት እንዲያስፈጽም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ለእቅዱ ተፈጻሚነት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ ማቅረባቸውን የሀረሪ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡