በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 1 ሺሕ 800 ጀሪካን የምግብ ዘይት ተያዘ

ሚያዝያ 7/2014 (ዋልታ) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 1 ሺሕ 800 ጀሪካን ባለ 3 ሊትር የምግብ ዘይት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ዘይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ፉሪ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
ዘይቱን ሲያጓጉዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-43648 አ.አ የሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሕጋዊነቱን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ሰነድ ባለመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሦስት ተጠርጣሪዎች እንደተያዙም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት እና የምርት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አንዳንድ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኅብረተሰቡ የፀጥታ አካላቱን በመደገፍ እያደረገ ላለው ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።