በመስኖ ልማት 311 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ ተገለፀ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) በአገር ደረጃ በመስኖ ሥራ 311 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን መንግሥት ገለፀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ በሽብር ቡድኑ ነፃ በወጡ አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ የመኸር ምርትን በአግባቡ ለመስበሰብና የመስኖ ልማት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በመስኖ ሥራው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለማግኘት መንግሥት አበክሮ እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአገር ደረጃ በመስኖ ሥራ 311 ሺሕ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አሳውቀዋል፡፡

በበጋ የመስኖ ስንዴ በአጠቃላይ 16 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አገር ራስን ችሎ ለመቆም የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ስላለው መንግሥት በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም አረንጓዴ አሻራ ለምግብነት በሚውሉ ፍራፍሬዎችም ጭምር ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት፤ ጦርነቱ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ መሸከም እንዲቻል ግብርናውን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዚህም በ2014 በጀት ዓመት 17 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ለመገንባት 9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸው አሁን ላይ 12 ፕሮጀክቶች ወደተግባር መግባታቸውን አሳውቀዋል።