በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር የተመራ ልዑክ በሶማሌ ክልል የልማት ሥራዎችን ጎበኘ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አይሻ መሐመድ የተመራ እና የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተ ቡድን ዛሬ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እየተካሄዱ የሚገኙ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ዑስማን በክልሉ ያለውን ለም መሬትና የውሃ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከፌደራል መንግሥት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሚኒስትሯ ተመራው ቡድን በሲቲ ዞን አዲጋላ ወረዳ ለመስኖ የተዘጋጁ የመሬት ዝግጅቶች እና እየፈሉ የሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ተመልክቷል፡፡
የሶማሌ ክልል ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች መካከል የሲቲ ዞን አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ በከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ከታደሉ አካባቢዎች በዋናነት ይጠቀሳል። ዞኑ ከጎረቤት አገር ጅቡቲ ጋርም የሚዋሰን መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።