በመተከል ዞን የነበረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት እርቀ ሰላም ተካሄደ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በመተከል ዞን የነበረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት ”ከልብ የመነጨ እርቅ ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በግልገል በለስ ከተማ በባህላዊ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ክዋኔ እርቀ ሰላም ተካሄደ፡፡
በእርቀ ሰላም ፕሮግራሙ ላይ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ወጣቶች፣ በድርጊታቸው የተጸጸቱ የተሃድሶ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የጉሕዴን አባላት፣ የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ወጣቶች በተሃድሶ ስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር ከሕዝቦች ጋር የነበረውን አብሮነት በማጠናከር ወደ ልማት ለመግባት የተደረገውን እርቀ ሰላም ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በመተከል ዞን ትጥቅ በመፍታት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ እርቀ ሰላም የፈጸሙ የጉሕዴን አባላት ማንዱራ፣ ድባጤ፣ ቡለን፣ ወምበራና ዳንጉር ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ ናቸው።
በእርቀ ሰላም ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ የጠላትን አጀንዳ ከማስፈጸም በመቆጠብ የሰላምን አስፈላጊነት ለሌሎች ግለሰቦች ግንዛቤ በመስጠት ወደ ሰላም ተመልሰው ይቅርታና ምህረትን በእርቀ ሰላም በመፍታት ወደ ልማት መግባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የይቅርታና ምህረት ፕሮግራሙ በጉሙዝ ብሔረሰብ ዘንድ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚታወቀው ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ክዋኔን መሰረት በማድረግ የተካሄደ መሆኑን የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።