መስከረም 12/2014 (ዋልታ) የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዥን ፒንግ ዋጋ ለሌለውና ለዜሮ ድምር ጨዋታ የሚደረግን የውስን አካላት መሰባሰብ በመቃወም፤ የተባበሩት መንግሥታት በተወሰነ ቡድን ወይም አገር ሊጋለብ አይገባም ሲሉ አሳሰቡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለተባበሩት መንግሥታት 76ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ለሰው ልጆች ሁሉ የጋራ እሴት የሆኑትን ሰላም፣ ልማት፣ ርትዕ፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና ነፃነትን መስበክ አለብን ያሉ ሲሆን፤ ዋጋ ለሌለውና ለዜሮ ድምር ጨዋታ የሚደረግን የውስን አካላት መሰባሰብም ማስቀረት አለብን ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲ ሁሉም አገራት እንዲቀዳጁት የሚጠበቅ እንጂ ለአንድ አገር ብቻ የተሰጠ ልዩ መብት አይደለምም ብለዋል፡፡
ቻይና አሜሪካ ውድቀት ካስመዘገበችበት የአፍጋኒስታን ቆይታ ጋር በተያያዘ በሰጠቻቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች የዴሞክራሲ መምህር እኔ ነኝ በሚል እብሪት በአገራት የውስጥ ጉዳይ ዘሎ የመግባትን ፍላጎት መቃወሟ ይታወሳል፡፡
ሩሲያና ቻይና በዴሞክራሲ ስም የመልካ ፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት መጣርንም መቃወማቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቀድሞ በተቀረፀውና ለመንግሥታቱ ጉባኤ በቀረበው ንግግራቸው አክለው የአንድ አገር ስኬት የሌላው አገር ውድቀት አይደለም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ዓለም የሁሉንም አገራት ልማትና እድገት የሚችል አቅም አላት ነው ያሉት፡፡
የተባባሩት መንግሥታትን በተመለከተም ባደረጉት ንግግር ተቋሙ እውነተኛ የብዝኃነት መገለጫ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ተቋሙ አንድ አገር ወይም የተወሰነ ቡድን ሊጋልበው ሳይሆን ሁሉም አገራት የዓለምን ደኅንነት፣ የጋራ እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ በጋራ ሊወስኑ የሚገባበትን ጥብቅ ሕግ መጠበቅ አለበት ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡