ሰኔ 07/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ስራ ተቋራጮች እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የምስጋና እና የእውቅና መርኃግብር ተካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጀት ዓመቱ በከተማዋ ከሰባት በላይ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በትላንትናው ዕለት ከማዘጋጃ ቤት – የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት በይፋ መመረቁን ገልጸው፣ በአጠቃላይ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ2 ሺህ 500 በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳደግ ባለፈ ገጽታን በመቀየር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በጠቅላላው ከተያዘው 61 ቢሊየን ብር ከ33 ቢሊየን ብር በላይ ለልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች መዋሉንም አስታውቀዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባዋ፣ የመጣውን ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱም ለነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ ስራ ተቋራጮች በተለይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ሊመሰገኑ እና ሊበረታቱ እንደሚገባም አመልክተዋል።