በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጎበኙ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጎበኙ።

ከተለያዩ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

የታላቁ ቤተመንግስት የመኪና ማቆሚያ፣ የየካ ቁጥር-2 መኪና ማቆሚያ፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል፣ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር በጋዜጠኞቹ ተጎብኝቷል።

የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ማቋቋሚያ፣ የኮልፌ የገበያ ማዕከል እና የዘውዲቱ ሆስፒታል ማስፋፊያ የግንባታ ሂደትም በጋዜጠኞቹ ተጎብኝቷል።

በዚህም ግንባታቸው የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል ከ93 በመቶ በላይ፣ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር 95 በመቶ፣ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ማቋቋሚያ የኮልፌ የገበያ ማዕከል 91 በመቶ መድረሳቸው ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ጠይባ ሉና በ2014 በጀት ዓመት ከ300 በላይ የግዙፍ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጠናቀቁን አስታውሰው በዘንድሮው ዓመትም በርካታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታም በማጠናቀቂያ፣ በግንባታ እና በጅማሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ኃላፊዋ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከፕሮጀክቶች ግንባታ በተጨማሪ በስራ እድል ፈጠራ፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንዲሁም ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW