በመዲናዋ የመከላከያ ሠራዊቱን ለተቀላቀሉ ዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው

ነሐሴ 23/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በመዲናዋ የመከላከያ ሠራዊቱን ለተቀላቀሉ የዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም የጀመረው ጸብ አጫሪነት በርካቶችን ለችግር ዳርጓል።

የሽብር ቡድኑ አሁን ደግሞ በአፋር እና አማራ ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ መንግስት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።

በዚህም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ሀገራቸው ያቀረበችላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የሽብር ቡድኑን የጥፋት ተልእኮ ለመመከት ዘምተዋል።

ይህንንም ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ዘመቻውን ተቀላቅለዋል ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ወጣት ታምራት ሚሊዮን እንዳዳለው የዘማች ቤተሰቦችን የመደገፍና የማበረታታት ስራዎችን እየተሰራ ይገኛል።

ማህበሩ የዘማች ቤተሰቦችን ቤት በማደስና የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጸው።

እነዚህን ቤተሰቦች ብቸኝነት እንዳይሰማቸው የመንከባከብ እና ከጎናቸው መቆም የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑንም ወጣት ታምራት ተናግሯል።

ማህበሩ በመጪው አዲስ ዓመት ዕለት ከዘማች ቤተሰብ ጋር እንደሚያሳልፍም ነው የተናገረው።

የመዲናዋ ነዋሪዎች የዘማች ቤተሰቦች በመንከባከብ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም  ጥሪ አቅርቧል።

የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ማቲዮስ ብርሀኑ በበኩሉ የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር ያቀኑት ዜጎች ዋነኛ ዓላማ የሀገር ህልውናን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሶ፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ ለዘማች ቤተሰቦች እገዛ የማድረግ የዜግነት ግዴታ አለበት ብሏል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በመዲናዋ የ46 የዘማች ቤተሰቦችን ቤት አድሰናል ነው ያለው።

በአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የምክር ቤት አባል ወጣት አብዱራህማን ካሱ፤ ማህበሩ የዘማች ቤተሰቦችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የዘማች ቤተሰቦች መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ እንዲያሳልፉ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያውያን “ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም፣ በምንም!” በሚል መሪ ሃሳብ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።