በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረጉ

ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ያሰባሰበውን የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርትኳን አያኖ ለሚመራው የልዑካን ቡድን ማስረከቡ ነው የተገለጸው።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ቄስ ፍራንሲስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኮሚቴው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለመመከትና ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ሃብት ለማሰባሰብ መመስረቱን ገልፀዋል።

ኮሚቴው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃብት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ከልዩ ልዩ አካላት ጋር በመተባባርና የአሜሪካ ምክር ቤት ተመራጮችን በማግባባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ስራዎችንም በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሚኔሶታ የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር አብዱላዚዝ መሐመድም በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከፍተኛ ሃብት በማሰባሰብ የሃገር ባለውለታነታቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ሳይወሰኑ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በሃገር ውስጥ የቀጥታ ኢንቨስትመንት እያሳዩት ያለው ተሳትፎም የሚበረታታ እንደሆነ ነው አምባሳደሩ የገለፁት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው፣ በሚኔሶታና ሚድዌስት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኮቪድ-19 ምክንያት በችግር ውስጥ ባሉበት ሁኔታ እንኳ ሃገራቸውን ለማገዝ እያደረጉ ስላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።