በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የፀጥታ መዋቅር ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል በሕገ ወጥ መንገድ የተደበቁ የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገለፀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ኃይሌ ብርሃኑ እንደተናገሩት በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የተደበቁ 397 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች፣ 60 የክላሽ ጥይት፣ 13 የክላሽ ሰደፍ እንዲሁም አንድ ክላሽ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ሽጉጡ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጠረፍ ወርቅ በተባለ ቀበሌ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ላይ በኅብረተሰቡና በፀጥታ መዋቅሩ ክትትልና ፍተሻ በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ነው ረዳት ኢንስፔክተር ኃይሌ የገለጹት።

ወቅቱ የተደቀነብንን የኅልውና አደጋ በጋራ የምንመክትበት እንጂ ለጠላት ምቹ ሁኔታ የምንፈጥርበት አይደለም ያሉት ረዳት ኢንስፔክተሩ በሕገ ወጥ ንግድ እና መሣሪያ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።