በምዕራብ ኦሞ ዞን በሱሪ እና ቤሮ ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች እርቀ ሰላም ተካሄደ

ሚያዝያ 3/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን በሱሪ እና ቤሮ ወረዳ አጎራባች ቀበሌዎች እርቀ ሰላም ተካሄደ፡፡
እርቀ ሰላሙን ያስፈጸሙት የአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎች በጀባ ቡርጂ ባህላዊ ሥርዓት ከበቀል ይልቅ ይቅርታን ማስቀደም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ጎጂ ልማዳዊ የጋብቻ ጥሎሽ ሥርዓት የክፍያ መጠን በመቀነስ፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመቆጣጠር እና ወንጀለኞችን ለህግ በማጋለጥ እንደ ቀድሞው በሰላም መኖር ይገባናልም ነው ያሉት፡፡
የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከበደ ቡርጂ ሁለቱ ሕዝቦች በጋራ አብረው ማደግ የሚችሉበት ሰፊ ፀጋ ያለው ምድር ላይ ቢኖሩም በሰላም እጦት ዓመታትን በስጋት እንደቆዩና በባህላዊ ሥርዓት በአባቶቻችን ወግ በተደረገው እርቅ ሰላማቸው ዳግም ተመልሷል ብለዋል።
የሱሪ ወረዳ ብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እያሱ ባምቡ መንግሥት የህግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝቦችን የሰላምና የልማት ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ በመሆኑ ይህ የዕርቅ ሂደት ውጤታማ መሆን እንደቻለ ገልፀዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ቢሰጥ ወርቁ በዞኑ ያሉ የሰላምና የፀጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር በአከባቢው ያሉ ሕዝቦችንና ሀገርን የሚጠቅሙ ሀብቶችን በተገቢው መንገድ ለመጠቀም ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በብሔር ካባ የሚሸሸጉ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት የህግ ማስከበር ሥራውን ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
አክሊሉ ሲራጅ (ከምዕራብ ኦሞ ዞን)