በምዕራብ ወለጋ ዞን በጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 21/2015 (ዋልታ) በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ለነበሩ ዜጎች ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የምዕራብ ወለጋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ነፃነት አለማየሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ከመመለሱ ጎን ለጎን በሰባት የዞኑ ወረዳዎች ከ6 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው ድጋፍ እያገኙ እንደሆነና ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፈው አንድ ወር ለነዚሁ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ5 ሚሊያን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።

ለተፈናቀሉት ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት የተሰበሰበ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ ድጋፉም መድኃኒት፣ የምግብ እህሎች፣ ብርድ ልብስ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የምግብ ዘይት፣ የልጆች ምግብና የእርሻ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ የተሰጠውም በዞኑ ቤጊ፣ ቆንዳላ፣ ላሎ አሳቢ፣ ቦጂ ድርመጂ፣ መና ሲቡና ቂልጡ ካራ ወረዳዎች ውስጥ በተለያየ መልኩ ተጠልለው ለሚገኙ ዜጎች ነው ብለዋል።

ድጋፉ ከተፈናቃይ ዜጎች በተጨማሪ ለቤጊ ጠቅላላ ሆስፒታል የሚውል የመድኃኒት ድጋፍ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የተደረገው ድጋፍ 5 ሚሊየን 743 ሺሕ 638 ብር ግምት ያለው እንደሆነም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ ያለው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ በመምጣቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመው ተፈናቃዮቹ ወደ መደበኛ ኑሯቸው ተመልሰው እስከሚቋቋሙ ድረስ ድጋፉ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።