በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

የካቲት 14/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለጀመረችው በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ላለፉት 29 ዓመታት በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ሲደግፍ የቆየው ሳሳካዋ አፍሪካ በግብርና ሽግግር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ እየመከረ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ተወካይ አብዱልሰመድ አብዱ መንግሥት የጀመረው ግብርናን የማሻገር ጉዞ እንዲሳካ እንደ ሳሳካዋ አፍሪካ ያሉ ባለድርሻ አካላት እገዛቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ ተሞክሮዎችን ለኢትዮጵያ ግብርና ያስተዋወቀው ሳሳካዋ አፍሪካ ግብርናው በሳይንሳዊ መንገዶች የተደገፈ እንዲሆን ከ9 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

በዚህም ከ2 ሺሕ 500 በላይ የግብርና ባለሙያዎችን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ማስመረቁ ታውቋል።

የሳሳካዋ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፋንታሁን መንግሥቱ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለጀመረችው የግብርና ሽግግር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

እንየው ቢሆነኝ (ከደብረ ብርሃን)