በሩብ አመቱ ከ400 በላይ ኢንተርፕራይዞች መቋቋማቸው ተገለፀ

ኅዳር 8/2015 (ዋልታ) በ2015 በጀት አመት ለማቋቋም ከታሰበው 4 ሺህ 62 ኢንተርፕራይዞች ውስጥ በሩብ አመቱ 4 መቶ 19 ኢንተርፕራይዞች መቋቋማቸው ተመላከተ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የ2015 በጀት ሩብ አመት አፈፃፀም መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልፈታ የሱፍ፤ በሩብ ዓመቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማልማት፣ ቀደም ሲል የተቋቋሙትንም ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።

ዘርፉ የስራ እድል በመፍጠር፣ የምርት መጠን በመጨመርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን በማዳን በኩል የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።

በመሆኑም መንግስት 38 ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለውን ገደብ እንደ ዕድል በመጠቀም ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርቶችን ላይ መስራት የሚገባ እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በ2015 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው።

በሰለሞን በየነ