በሩዋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ አሸነፉ

ፖል ካጋሜ

ሐምሌ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) ፖል ካጋሜ በሀገሪቱ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን የሩዋንዳ ምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

79 በመቶው ቆጠራ በተጠናቀቀው ብሔራዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ 99.1 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል።

ትላንትና በተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ የ66 ዓመቱ ፖል ካጋሜ ሁነኛ ተፎካካሪ አልነበራቸውም የተባለ ሲሆን አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከ11 ቀናት በኋላ ይፋ ይደረጋል።

በምርጫው የተሳተፉት የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቹ ፍራንክ ሃቢኔዝ እና ጋዜጠኛና ደራሲ ፊሊፕ ምፓይማና እስካሁን ባለው ቆጠራ ከ1 በመቶ ያነሰ ድምጽ ማግኘታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።

ከ14 ሚሊዮን ሩዋንዳዊያን 9 ሚሊዮን ያህሉ በምርጫው ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ2 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው የብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ካጋሜ በፓርቲያቸው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ዋና መስሪያ ቤት ባደረጉት ንግግር ሩዋንዳዊያን በሳቸው ላይ ስለጣሉት እምነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እ.ኤ.አ. ከ1994 የጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ የሀገሪቱ መሪ የነበሩት እና ከ2000 ጀምሮ ፕሬዝዳንት የነበሩት ካጋሜ ለአራተኛ ጊዜ በምርጫ ማሸነፍ ችለዋል።