በራህሌ ከተማና አካባቢዋ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) በጦርነት ምክንያት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ውድመት በመድረሱ ምክንያት ኃይል ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረው የበራህሌ ወረዳ ዳግም የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘቷ ተገለጸ፡፡

የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ያሲን አሊ አገልግሎቱን እንደገና ለመመለስ በተደረገ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ጥገና በወረዳው ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ወረዳዋ ከውቅሮ ሰብስቴሽን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ሲያገኙ የነበረ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱን ጠቅሰው በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ የነበሩ የመከከለኛና የዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመሮችን እና ትራንስፈርመሮች እንደገና በመጠገን አገልግሎቱ መመለስ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

ቀሪ በኪልበቲ ረሱ የሚያገኙ ከተሞች ለማገናኘት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈፃሚው በአካባቢዎቹ በመሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆት ማህበረሰቡና የመንግስት የፀጥታ አካላት በጋራ እንዲጠብቁ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።