በርካታ ፀረ ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን ፓርቲው አስታወቀ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) ባለፉት ቀናት በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ በርካታ ፀረ ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ፓርቲው ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች በስኬት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ስብሰባዎቹ በሀገራዊ የሰላምና ደኅንነት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ከውጭ ጉዳይና ዲፕሎማሲ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች በስፋት የተነሱበትና አቅጣጫ የተቀመጠባቸው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና አሸባሪው ሕወሓት ያሰማሯቸው ኃይሎች በንፁኃን ዜጎች ላይ ያደረሱትን እጅግ ዘግናኝ ግድያ ሁለቱ ኮሚቴዎች አውግዘው የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲካሄድ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ቀናት በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ በርካታ ፀረ ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን ጠቁመው ዘመቻው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች አላማቸው የመንግሥትና ሕዝብን የጋራ ትኩረት ማዛባት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ