በሰላም ሚኒስቴር 200 የሞተር ሳይክል ተሽከርካሪዎችን ለ6 ክልሎች ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – በሰላም ሚኒስቴር የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስተባበርያ 200 የሞተር ሳይክል ተሽከርካሪዎችን ለ6 ክልሎች ድጋፍ አደረገ።
በድጋፉ ለሱማሌ 72 ለአፋር 40 ለኦሮሚያ 36 ለደቡብ 18 ለቤንሻንጉል ጉሙዝ 18 ለጋምቤላ 16 ሞተር ተሽከርካሪዎችን ያሰራጨ ሲሆን ከስድስቱም ክልሎች የሚመለከታቸው ተወካዮች በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል።
በቆላማ አከባቢዎች የአርብቶአደሩን ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሠሩ መሆኑን በሚኒስቴሩ የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ አሳውቋል።
የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን በመጥቀስ በቅርብ ቀን 81 መኪኖች እንዲሁ በተጨማሪ ድጋፍ የሚደረጉ መሆኑን ዶ/ር ስዩም መስፍን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሰዒድ ዑመር በተጠቀሱት ስድስት ክልሎች በተለይም አርብቶአደሩ ማህበረሰብ በሚኖርባቸው ቆላማ አከባቢዎች የመንገድ መሠረተ-ልማት ተደራሽ ባልሆኑባቸው 100 ወረዳዎች ላይ የሚሠሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ለማሳለጥ እና በቂ አገልግሎቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ እንደነበር አስታውሰው ችግሩን ለማቃለል የሞተር ተሽከርካሪ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ማስተባበርያው ወደፊትም የሚያደርጋቸውን ድጋፎች የአርብቶአደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ በጥናት ተመስርቶ የሚያከናውን መሆኑን አቶ ሰዒድ ዑመር መግለፃቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።