በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ዲፕሎማቶች ስልጠናዊ ምክክር በበይነ-መረብ ተሰጠ

ግንቦት 06/2013 (ዋልታ) – በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኢምባሲ አምባሳደሮች ከከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር በመንግስት አገልግሎት ዘርፍ የ10 ዓመት ፍኖተ- ካርታ ሰነድ ላይ ስልጠናዊ ምክክር በበይነ-መረብ አካሂዷል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ስልጠናው በቀጣዩ አስር ዓመታት በህዝብ የሚመረጥ መንግስት የሚነድፋቸውን የልማት እቅዶች ማሳካት የሚችል የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ፣ ነፃ ገለልተኛና ብቃት ያለው የመንግስት አገልግሎት ስርዓት ለመገንባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም የመንግስት አገልግሎት ዘርፉን ለመለወጥ በርካታ የለውጥ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውንና በዚህም ለውጦች እንዳሉ ገልጸው፣ አሁን በሀገሪቱ የተጀመረውን መጠነ ሰፊና ትልልቅ የሪፎርም ፕሮግራሞች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የተዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ ተግባራዊ እንዲሆን በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በስልጠናው ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው ተቋም የመገንባት ሂደት፣ የሰው ሀብት የማልማት ስልት ከክህሎት ክፍተት ልየታ ተነስቶና በብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ታግዞ አቅም መገንባት፣ የመንግሥት ሠራተኞችን በጠንካራ ሥነ-ምግባር የታነጹ የማድረግና ዕሴት መገንባት እንዲሁም የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ግብ በበይነ-መረብ ወደሚቀርብበት ደረጃ ለማድረስ በመጀመሪያዎቹ የትግበራ ዓመታት ምቹ መደላደል መፍጠር ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።
መንግስት ዜጎች የሚጠብቀውን አገልግሎት በብቃት መስጠት እንዲችል የተዘጋጀውን የለውጥ ሰነድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅና ኢምባሲውም የለውጥ ማሻሻያ ፕሮግራሞቹ ወሳኝ በመሆናቸው ለተግባራዊነቱ የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ ስምምነት ላይ በመድረስ መጠናቀቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡