ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በሰሜን ኢትዮጵያ የግጭት ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች ለሚኖሩ 620 ሺሕ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የድርጅቱ የአፍሪካ ሕብረትና የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ቺሚምባ ዴቪድ ፊሪ እንደገለጹት ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው።
በተለይም መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ድርጅቱ ይደግፋል ብለዋል።
በዚህም የምግብና እርሻ ድርጅት በሰሜኑ ክፍል ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አንስተው የግብርና ሰብል ምርታማነት የበለጠ እንዲያድግ ተጨማሪ ድጋፎችን የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የእንስሳት ሀብት ልማት እንዲያድግ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል ክትባቶችን የሚያቀርብ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ድርጅቱ ተወካይ ገለጻ ድጋፉን ለማቀላጠፍ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።
ድርጅቱ በእስካሁኑ ሂደት በትግራይ ክልል ለሚገኙ 230 ሺሕ አርሶ አደሮች 400 ሜትሪክ ቶን ዘር ማድረሱን አንስተዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል 100 ሜትሪክ ቶን እንዲሁም በአፋር አራት ሜትርክ ቶን ዘር ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።
እንስሳትን ከበሽታ በመከላከል ሂደትም በትግራይ ክልል ለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንስሳት ክትባት የተሰጠ ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ 230 ሺሕ ለሚሆኑ እንስሳት የጤና አገልግሎት ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል ተወካዩ።
ድርጅቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለነዚሁ አካባቢዎች የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
”6 ሺሕ 700 ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በሂደት ላይ ነን፤ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈጸም እንጠብቃለን” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምንም እንኳን ድርጅቱ በሚችለው ሁሉ የግብርና ሥራ እንዲሻሻል ጥረት እያደረገ ቢሆንም የበጀት ውስንነት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በመንግሥት በኩል የተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አርሶ አደሮች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።