በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ከረቡዕ ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር ማስመለሱ ረቡዕ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ አስቸጋሪ ሁኔታ፣ በእስር ቤት እና በማዕከላት ውሰጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ብሔራዊ ፈፃሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሰራ ቆይተዋል።
16 የመንግሥት ተቋማትን በአባልነት የያዘው ፈፃሚ ኮሚቴው ዜጎችን ማስመለስ ለመጀር የተደረጉ የመጨረሻ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ዛሬ የገመገመ ሲሆን ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ ማስመለሱ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
የበረራ፣ የማቆያ ማዕከላት ዝግጅት፣ የመገልገያ ቁሳቁስ፣ የምግብ እና መጠጥ አቅርቦት፣ የአልባሳት፣ የትራንስፖርት እንዲሁም የህክምና አገልግሎትን ለተመላሾች በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ በማስቻል ረገድ የተደረጉ ዝግጅቶች በግብረ ኃይሉ አባላት ውይይት አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተመላሽ ዜጎች ካሉበት አምጥቶ እስከ መኖሪያ ቀያቸው የማድረስ ሥራን የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው ከመነሻው እስከ መድረሻው በተሳለጠ ቅብብሎሽ ለመፈፀም ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ተመላሾች አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ከየማዕከላቱ ክልሎች ቶሎ በማንሳት ወደ መኖሪያቸው መውሰድ ያለባቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ ያደረጉትን ዝግጅትም አቅርበው ውይይት ተደርጓል።
ያልተጠናቀቁ የዝግጅት ሥራዎችን በቀሪ ቀናት እንዲያጠናቅቁ ማሳሰባቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል ሚኒስቴር አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።
በየጊዜው የቅበላ አቅምን በማሳደግ ዜጎችን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት መንግሥት የተቻለውን ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።