በስፔን በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቱር ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸነፉ

የካቲት 24/2014 (ዋልታ) የወርቅ ደረጃ በተሰጠው እና ትላንት ምሽት በስፔን በተካሄደው ቪላ ዲ ማድሪድ የዓለም የቤት ውስጥ ቱር ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ድል ቀንቷቸዋል።

በዚህም በወንዶች 3 ሺሕ ሜትር ሰለሞን ባረጋ 7:34.03 በሆነ ሰዓት በመግባት አሸነፊ ሲሆን ለሜቻ ግርማ 7:37.09 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ፣ አዲሱ ይሁኔ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በሴቶች 1 ሺሕ 500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ 3:57.38 በሆነ ሰዓት በመግባት የቦታውን ሪከርድ ጭምር በማሻሻል አሸነፊ ሆናለች፡፡

በዚሁ መርሃ ግብር ሂሩት መሸሻ 4:02.22 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ 4:03.38 በሆነ ሰዓት በመግባት ሦስተኛ እንዲሁም አክሱማዊት አምባዬ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡

በሌላ በኩል አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3 ሺሕ ሜትር፣ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በ1 ሺሕ 500 ሜትር በ2022 በውድድር ርቀቶቹ በቱሩ ባስመዘገቡት ድምር ውጤት ቤልግሬድ ለሚደረገው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በቀጥታ ተሰላፊ የመሆን እድል ማግኘታቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡