በሶማሌ ክልል የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ አስችሏል – ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

ሚያዝያ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ አስችሏል ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።

የሶማሌ ክልል ለረዥም ዓመታት በግጭት ድባብ ውስጥ መቆየቱን አስታውሰው ከለውጡ በኋላ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ ሕዝቡ በሁሉም መስክ የልማት ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ጠቅሰው ከለውጡ በኋላ የግብርና ምርት ልማት በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።

በክልሉ ሁለት ዞኖች ብቻ ከ8 ቢሊዮን ብር ያላነሱ ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዝናብም ሆነ በበጋ መስኖ ልማት ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የስንዴና የሩዝ ልማት በስፋት እየተመረተ ይገኛል ብለዋል።

የምግብ ሰብሎችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉ እንቅሰቃሴ ደካማ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን ላይ ዘርፉን ማጎልበት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ለዘርፉ መነቃቃት የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንገድ፣ የውሃና የኃይል መሠረተ-ልማት ችግሮች በዘላቂነት ሲፈቱ የክልሉን ዕምቅ አቅሞች ለሀገራዊ ልማት ማዋል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።