በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ ተወሰነ

ነሐሴ 1/2014 (ዋልታ) በመጪው መስከረም ራስ ገዝ የሚሆነውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሳይጨምር በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ፒኤችዲ) እንደገለጹት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ትግበራው ለትምህርት ጥራት፣ በተቋማቱ መካከል የትብብር እና የፉክክር መንፈስ በማምጣት ልሕቀትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ጠቁመው በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲን ዕውን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ሲሆኑ ተወዳድረው ከውጭም ሀብት ያገኛሉ፤ ከአገር ውስጥ ከንግዱም ማኅበረሰብ በምርምርና በማማከር ገቢ ያስገባሉ፤ ብቁ ተማሪ ስለሚያወጡ ከመንግሥትም ተጨማሪ በጀት ያገኛሉ።
ውድድሩ ልህቀት ያመጣል፤ የትምህርት ልህቀት በአገር ውስጥ አይገደብም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
ለመምህራኖቹ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም አሟልተው እንዲቀጥሩ የሚያስላቸው እንደሚሆን ጠቁመው ለሚቀጥሯቸው መምህራን እንደ አቅማቸው የሚከፍሉበት ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ምሁራኖቹ በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በማስተማር፣ የጥናት ጽሑፎች በማዘጋጀት ከውጭ በሚያስገኙት ሀብት መሠረት አድርገው እንደልፋታቸው እንዲከፈላቸው ያስችላል ሲሉም ገልፀዋል።
‹‹በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፤ ዩኒቨርሲቲን በሰፈር አጥረነው መቀጠል የለብንም፤ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ በመሆኑም ራስ ገዝነት በጣም ወሳኝ ነው›› ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።