በቅርቡ ድላችንን እንዘምራለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) አሸባሪውን ሕወሓትና ተላላኪዎቹን እስከወዲያኛው በማሰናበት በቅርቡ ድላችንን እንዘምራለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
በመስቀል አደባባይ አሸባሪዎቹን ሕወሓት እና ሸኔን የሚያወግዝና መከላከያ ሰራዊትን እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ ኃይሎችን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው፡፡
በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው አሁን ላይ እየነጋ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በቅርቡ በዚሁ ስፍራ ተሰብስበን ድላችንን እንዘምራለን ሲሉ ነው አሸባሪው ሕወሓትና አጋሮቹ የመጨረሻው የሞት አፋፍ ላይ መድረሳቸውን የገለፁት፡፡
ካንቲባዋ የሽብር ቡድኑ ከገባበት እንዳይወጣ ይደረጋል ያሉም ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ሃብታቸውን ኢትዮጵያን ለማዳን የመጨረሻው ምዕራፍ እንዲያውሉትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡