በባሕር ዳር ነገ በተመጣጣኝ ዋጋ የዘይት ሥርጭት ይካሄዳል

የካቲት 27/2014 (ዋልታ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በነገው ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመጣጣኝ ዋጋ የዘይት ሥርጭት እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት በአገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ቢሆኑም በኅብረተሰቡ ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በምግብ እህሎችና የምግብ ዘይት ላይ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ነው አስተዳደሩ የገለጸው፡፡

መንግሥት ይህንን ለማረጋጋት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ችግሩን ለመቀነስ በከተማ አስተዳደሩ ሁለት መሠረታዊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በዚህ መሰረትም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ ባደረገው አስችኳይ ስብሰባ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን 10 ሚሊየን ብር ተዘዋዋሪ ብድር በጀት በመመድብ የግብርና ምርቶችና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተለይም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም በበላይነህ ክንዴ ለከተማችን የሚቀርበው የፊቤላ ዘይት በወቅቱና በበቂ መጠን እየቀረበ ባለመሆኑ ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር በመነጋገር 883 ሺሕ ሊትር ፓልም ዘይት ከውጭ ተገዝቶ በአለ በጅምላ በኩል መቅረቡ ነው የተጠቆመው፡፡

በነገው ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የዘይት ሥርጭት እንደሚካሄድ መገለጹን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡

በከተመዋ ከነገ ጀምሮ መሰራጨት የሚጀምረው ፓልም ዘይት መግዣና መሸጫ ዋጋም መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከቸርቻሪዎች/ሸማቾች ህ/ስ/ማ ከአለ በጅምላ የሚገዙበት የጅምላ ዋጋ

  • ባለ 20 ሊትር 1575.6 ብር ፣ ባለ 5 ሊትር 408.6 ብር፣ ባለ 3 ሊትር 251.10 ብር ሲሆን፣

ከቸርቻሪዎች/ሸማቾች ህ/ስ/ማ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚያሰራጩበት ዋጋ ደግሞ፡-

  • ባለ 20 ሊትር 1641.80 ብር ፣ባለ 5 ሊትር 425.80 ብር፣ ባለ 3 ሊትር 261.70 ብር