በቤተ ክርስቲያኗ አስተባባሪነት በሲዊዲን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ተፈጸመ

ግንቦት 10 /2013 (ዋልታ) – በስዊድንና በስካንዲኔቪያን ሀገሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት አስተባባሪነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ ተፈጸመ።
የስዊድንና የስካንዲኔቪያን ሀገሮች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በድጋሚ “አለን ለዓባይ በማለት” የቤተክርስቲያኗን አማኞች ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በስዊዲን የኢትዮጵያ የኤምባሲ ተወካዮች በተገኙበት የ5 ሺህ 800 የአሜሪካ ዶላር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ፈፅመዋል።
በዚህ ወቅት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ባስተላለፉት መልዕክት “በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈታኝ ጊዜ እያሳለፈች ትገኛለች፣ ጠላት ከውስጥም ከውጭም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሀገራችንን ጫና ውስጥ ለማስገባት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትጵያውያን በአንድ ላይ መተባበር ይገባል” በማለት አሳስበዋል።
የግድቡ የሁለተኛ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እውን እንዲሆን መላው ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን በማጠናከር በቦንድ ግዢ፣ በስጦታ፣ ባለው ሙያና እውቀት ሁሉ ሀገሩን በማገዝ ታሪክ ለመሥራት በአንድ ላይ መነሳት እንደሚያስፈልግም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን በሲውዲን የኢትዮጵያን ኤምባሲ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል ፡፡