በቤንች ሽኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ባህላዊ የዕርቅ ስርዓት ተከናወነ

የካቲት 12/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል ቤንች ሽኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ሳንቃ ቀበሌ ባህላዊ የዕርቅ ስርዓት ተከናውኗል፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አሰተዳደሪ አቶ ፍቅሬ አማን በዕርቀ ሠላም ፕሮግራሙ ላይ እንደገለፁት ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩትን ሠላም እና የአብሮነት ዕሴት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባዋል።

ለዘመናትም አብረው በወንድማማችነትና በአንድነት ተሳስሮ በኖርው ማህበረሰብ መካከል ልዩነትና ጥርጣሬ እንዲኖር የሚያደርጉትን አካላት በመገሰፅና በመምከር ረገድ አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ወደ ልማታቸው ፊታቸውን መልሰው ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።

የአካባቢውን ገፅታና የበርካቶችን ህይወት ሊቀይር የሚችል የሚዛን ቴፒ አስፋልት መንገድና ሌሎች የህብረተሰቡ ልማቶች በፀጥታ ችግር መጎዳታቸውን የጠቆሙት አቶ ፍቅሬ ህብረተሰቡ ይህን በመረዳት ለሠላም መጠበቅ የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል ብለዋል።

የአካባቢው ሠላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሀገር ሽማግሌዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ላደረጉት በጎ ተግባር ሊመሰገኑ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ሠላምና አንድነትን ማምጣት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ዘንድ የሚጠብቅ ግዴታ እንደሆነ የጠቆሙት ደግሞ የሸኮ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ አቶ ቤርጉ ፆማ ናቸው፡፡

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለመፍታት ከሠላም አምባሳደሮችና ሚሊሻዎች ጋር የጀመሩትን ስራ አጠናክርው እንደሚያስቀጥሉም አስረድተዋል።

አቶ ቤሩ ጎበናና ቄስ አይመሮ አንተነህ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው እርቀ ሰላሙ በተፈጠረው አለመረጋጋት አካባቢያቸውን ለቀው የነበሩት ነዋሪዎች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ ከማስቻሉም ባሻገር ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ዕርቀ ሰላም መካሄዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልፀዋል።
(ምንጭ፡-ደሬቴድ)