በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) ብሔራዊ ጥቅሞችን ለይተን በማወቅ ኅብረትን እና የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ለኅብረታችን” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሂዷል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ሚኒስቴሩ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምን ለማንም እና በምንም ሁኔታ አሳልፎ አይሰጥም፤ ይህንንም በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለይተን በማወቅ ኅብረታችንን ማጠናከርና የውስጥ አንድነትን አጠናክሮ ለችግሮች መፍትሄ ለመሻት ብሔራዊ ጥቅም ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ሲሉም ገልፀዋል።

ሀገራዊ ድንበር፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ፣ የአርንጓዴ አሻራ፣ የቀጣናው የፖለቲካ ሁኔታ፣ ታሪክ፣ ፌዴራሊዝምና ብዘኃነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ ኡስማን (ፒኤችዲ) ዩኒቨርሲቲዎች የሀሳብ፣ የእውቀትና ፍልስፍና መፍለቂያ በመሆናቸው በአሉቧልታና በወሬ ሰላማቸው የሚናጋ ሳይሆኑ በምክንያታዊነትና በውይይት መግባባት የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።

ሀገር ኅልውናዋ እንዳይናጋ የብሔራዊ ጥቅሟን በግልፅ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባትም ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅም አወዱ የሚለያይ ቢሆንም ፖለቲከኞች ሀገር ካለችበት ወቅት አንፃር ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስከብሩ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አካሉ ጴጥሮስ (ከሰመራ)