በተለምዶ “ሿሿ” የተባለውን የስርቆት ወንጀል ፈፅመው ሊሰወሩ የነበሩ 8 ግለሰቦች ተያዙ

የሰኔ 14/2014 (ዋልታ) ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ እና ተሳፋሪ በመምሰል በተለምዶ “ሿሿ” የተባለውን የስርቆት ወንጀል ፈፅመው ሊሰወሩ የነበሩ 8 ግለሰቦች በፖሊስና በኅብረተሰቡ ትብብር ተይዘው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ቅድስት ማርያም አካባቢ ነው።
ከ6 ኪሎ አቅጣጫ የመጣ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-36245 አ/አ የሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ነጠላ እና ፎጣ የተከናነቡ 4 ሴቶች እና 4 ወንዶችን ተሳፋሪ በማስመሰል በግብራበርነት የሚሳተፉ ግለሰቦችን ጭኖ ወንጀል ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ነበር።
ቅድስት ማርያም አካባቢ ሲደርሱ ትራንስፖርት በመጠባበቅ ላይ የነበረችውን የግል ተበዳይ ወዴት እንደምትሄድ ከጠየቋትና ወደ ሜክሲኮ እንደምትሄድ ከነገረቻቸው በኋላ ግቢ ብለው በማስገባት ከሹፌሩ ኋላ ባለው ወንበር ላይ እንድትቀመጥ ያደርጓታል።
ከጎኗ የተቀመጠችው ሌላኛዋ ተጠርጣሪ ስልክ የምታወራ በማስመሰል እና የግል ተበዳይ ምን ዓይነት ስልክ እንደያዘች ለማረጋገጥ ስልክ ቁጥር ያዢልኝ ብላ ስልኳን ከተመለከተች በኋላ ወንበር ቀይሪ ሌላ ተሳፋሪ ልንጭን ነው በማለት ወደ ጋቢና ያስገቧታል።
ጋቢና ከገባች በኋላ አሽከርካሪው በተራው የትራፊክ ፖሊስ እንዳይቀጣኝ ቀበቶ ማሰር አለብሽ ብሎ ራሱ ሊያስርላት በመሞከር እና በሩም በደንብ አልተዘጋም ልዝጋው በማለት ካዋከቧት በኋላ ከቦርሳዋ ውስጥ የዋጋ ግምቱ 7 ሺሕ ብር የሚያወጣ የሞባይል ስልክ በመውሰድ ገፍትረው ከተሽከርካሪው ማስወረዳቸውን በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከጃንሜዳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተገፍትራ ከተሽከርካሪው የወደቀችው የግል ተበዳይ ባሰማችው የድረሱልኝ ጩኸት ተጠርጣሪዎቹ ከነተሽከርካሪው በአካባቢው በነበሩ የፖሊስ አባላት እና በኅብረተሰብ ትብብር እጅ ከፍንጅ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የጃን ሜዳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል።