በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የኮሌራ፣ ወባና ኩፍኝወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

ዶ/ር መቅደስ ዳባ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የኮሌራ፣ የወባ፣ ኩፍኝና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

“ጠንካራ የማህበረሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ” በሚል የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ማጎልበት ላይ ያተኮረ ንቅናቄ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደሀገር የጤና አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ወረርሽኞችን በአፋጣኝ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ወሳኝ እንደሆነ አመላክተዋል።

በተለይም የሚከሰቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም የሚከሰቱ ወረርሽኞች በተወሰኑ አካላት ብቻ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የማይቻል በመሆኑ በወረርሽኞች ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

“ፅዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” በሚል ቃል የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄም የጤና ዘርፉን ለማሳደግ ጉልህ ማና ያለው በመሆኑ ሁሉም በንቃት መሳተፍ ይገባል ነው ያሉት።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ለሚከሰቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የበጀት ችግርን መቅረፍ እንደሚያስፈልግና ለንቅናቄው መሳካትም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው 19 ነጥብ 6 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ስርጭት ማድረግ መቻሉን ጠቁመው በ400 ወረዳዎች ለተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ምላሽ በመስጠት በ320 ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉንና በቀሪዎቹ ደግሞ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ንቅናቄው ለህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም በዋናነት ስለህብረተሰብ ጤና አደጋ ሁኔታዎችን በማሳወቅና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ለሚከሰቱ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑን ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ”ለፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ጥሪ ምላሽ የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)